ውጤታማ የስራ አመራር ስልጠና በኦስሎ ማህደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ተሰጠ
በኦስሎ ማህደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ለአምስት ተከታታይ ሳምንታት በበይነ መረብ የተሰጠው የውጤታማ ስራ አመራር ስልጠና በትናንትናው ዕለት ሚያዝያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ተጠናቀቀ። በስልጠናው የተካተቱ የይዘት አርእስት የኢ/ኦ/ተ/ቤ፣ ባህል እና የለውጥ አመራር፣ ውጤታማ ተግባቦት፣ ውጤታማ ስብሰባ፣ በእቅድ መመራት፣ የአሰራር መመሪያ ዝግጅት እና ውጤታማ የጊዜ አጠቃቀም ሲሆኑ ስልጠናው በአጥቢያ ዶት ኮም ባለሞያዎች በሚሰጥ ገለጻ፣ ሰልጣኞችን ያሳተፈ ውይይት እና ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን ያካተተ እንደነበረ ታውቋል።
የደብሩ አስተዳዳሪ ቀሲስ ተስፋ ሚካኤል መኮንን በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ ገልጸዋል። ስልጠናው ብዙ ክህሎቶችን ያስጨበጠ ሲሆን በቀጣይም ወደ ትግበራ በመቀየር የአሰራር ማሻሻያዎችን ማስመግዘብ ይገባናል ብለዋል። በተጨማሪም በጅማሮ ላይ ያለው የደብሩ ስልታዊ እቅድ ዝግጅት ከአጥቢያ ዶት ኮም በሚደረገው ሞያዊ ድጋፍ የደብሩን ማኅበረሰብ አሳታፊ በሆነ መልኩ በልጽጎ ስራ ላይ እንዲውል እንሰራለን ብለዋል።
አጥቢያ ዶት ኮም በቀጣይ የክፍሎች አሰራር መመሪያዎች ዝግጅት እንዲሁም የቴክኖሎጂ ክፍልና የማዋቀር እና ስራ የማስጀመር ፕሮጀክቶችን ከደብሩ ሰበካ አስተዳደር ጉባኤ ጋር በመሆን የሚተገብር መሆኑም ተገልጿል።