በስዊዘርላንድ ለሚገኙ የሕጻናት እና አዳጊዎች ክፍል አገልጋዮች የውጤታማ ሥራ አመራር ስልጠና ተሰጠ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ ፀሐየ ጽድቅ መድሃኔዓለም ቤተክርስቲያን ጄኔቫ የአዳጊ ወጣቶች መንፈሳዊ ትምህርት ቤት አስተባባሪነት በስዊዘርላንድ ለሚገኙ የሕጻናት እና አዳጊዎች ክፍል አገልጋዮች በአጥቢያ ዶት ኮም የተሰጠው የውጤታማ ሥራ አመራር ስልጠና መጋቢት 22 ቀን 2018 ዓ.ም. (ማርች 31፣2026) ተጠናቋል።

ስልጠናው በ 6 መርሐግብሮች የተሰጠ ሲሆን የተሸፈኑት ዋና ዋና አርእስት የለውጥ አመራር፣ ኦርቶዶክሳዊ ሥራ አመራር፣ የሥራ መመሪያ፣ ውጤታማ ተግባቦት እና ውጤታማ ስብሰባ፣ እቅድ፣ ትግበራ፣ ክትትል እና ግምገማ እንዲሁም በቴክኖሎጂ የተደገፈ ሥራ አመራር እንደሆኑ ተገልጿል። ስልጠናው በገለጻ፣ በውይይት፣ መነሻ ሰነዶችን በማቅረብ እንዲሁም በተግባራዊ እንቅስቃሴ (የቤት ሥራ) የታገዘ አፈጻጸም የነበረው ሲሆን ይህም ተሳታፊዎች የሚቀርብላቸውን መነሻ ይዘት ለመተግበር እና በግላቸው በጥልቀት ለመከታተል እድል የሰጠ ሆኗል።

የስልጠናው አስተባባሪ ፀሐየ ጽድቅ መድሃኔዓለም ቤተክርስቲያን ጄኔቫ የአዳጊ ወጣቶች መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ከስልጠናው የተገኙ መነሳሳቶችን እና ጅማሮዎችን በሕብረት እና በመናበብ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ያሳወቀ ሲሆን ስልጠናውን የሰጠውን አጥቢያ ዶት ኮምን አመስግነዋል። በቀጣይም የአተገባበር ክትትል እና እገዛ እንዳይለያቸው አደራ በማለት መርሐግብሩ ፍጻሜን አግኝቷል።