“Atbiya App – አጥቢያ” የአንድሮይድ መተግበሪያ ተለቀቀ

አጥቢያ ዶት ኮም “ቴክኖሎጂ ለቤተክርስቲያን” በሚል መሪ ቃል ልዩ ልዩ የቴክኖሎጂ ስራዎችን እያበረከተ ይገኛል። የአገልግሎቱን ተደራሽነት ለማሳደግ ያግዝ ዘንድ “Atbiya App – አጥቢያ” የተባለ የአንድሮይድ መተግበሪያን በማዘጋጀት በጉግል ፕሌይ ስቶር ላይ ለተጠቃሚዎች የተለቀቀ ሲሆን የመተግበሪያው የመነሻ ይዘቶች፡
– ግጻዌ፦ ቀን መቁጠሪያ እና የእለት ምንባባት
– ወቅታዊ ይዘቶች፦ በቤተክርስቲያናችን ልዩ ልዩ ይፋዊ ድረገጾች የሚለቀቁ ወቅታዊ ይዘቶች
– የጸሎት መጻሕፍት

በተጠቃሚዎች አስተያየት እና ጥቆማ ለወደፊት ተጨማሪ ይዘቶች እንደሚለቀቁ ታውቋል። የአንድሮይድ መተግበሪያውን ከዚህ በታች ባለው አድራሻ ማግኘት ይቻላል።
https://play.google.com/store/apps/details?id=com.atbiya.atbiya

ውጤታማ የስራ አመራር ስልጠና በትሮንዳሔም ምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ተሰጠ

በኖርዌይ ትሮንዳሔም ምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ለስድስት ተከታታይ ሳምንታት በበይነ መረብ የተሰጠው የውጤታማ ስራ አመራር ስልጠና በትናንትናው እለት ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም. ተጠናቀቀ። በስልጠናው የተካተቱ የይዘት አርእስት የኢ/ኦ/ተ/ቤ፣ ባህል እና የለውጥ አመራር፣ ውጤታማ ተግባቦት፣ ውጤታማ ስብሰባ፣ በእቅድ መመራት፣ የአሰራር መመሪያ ዝግጅት እና አገልግሎት ሲሆኑ ስልጠናው በአጥቢያ ዶት ኮም ባለሞያዎች በሚሰጥ ገለጻ፣ ሰልጣኞችን ያሳተፈ ውይይት እና ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን ያካተተ እንደነበረ ታውቋል።

የደብሩ አስተዳዳሪ መጋቤ ብሉይ አባ ቀለመወርቅ አቡኔ በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ የገለጹ ሲሆን ስልጠናው ብዙ ጉዳዮችን የሸፈነ እንደመሆኑ ወደ ትግበራ በመቀየር የሚጨበጥ ውጤቶችን ማስመግዘብ ይገባናል ብለዋል።

አጥቢያ ዶት ኮም በቀጣይ የክፍሎች አሰራር መመሪያዎች ዝግጅት እንዲሁም አሰራሮችን በቴክኖሎጂ የማስደገፍ ፕሮጀክቶችን ከደብሩ ሰበካ አስተዳደር ጉባኤ ጋር በመሆን የሚተገብር መሆኑም ተገልጿል።

የሕጻናት እና አዳጊዎች ክፍል ውስጣዊ አሠራር መመሪያ በሸገር ከተማ ሃገረ ስብከት ደ/ኃ/ቅ/ሚካኤል ካቴድራል ፍሬ ስብሐት

በአጥቢያ ዶት ኮም ትብብር የተዘጋጀው የሕጻናት እና አዳጊዎች ክፍል ውስጣዊ አሠራር መመሪያ በሰንበት ት/ቤቱ ሥራ አመራር ጸድቆ የሙከራ ትግበራ ለማስጀመር ዝግጅት እንደተጀመረ ተገለጸ። የመመሪያ ዝግጅቱ በሕጻናት እና አዳጊዎች አገልግሎት ሱታፌ ያላቸው ልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ሲሆን በዋናነት ከወላጆች መረጃዎችን በመጠይቅ እንዲሰበሰብ መደረጉ ታውቋል።

የተዘጋጀው መመሪያ በሙከራ የትግበራ ጊዜው የሚገኙ ልምድ እና ግብአቶችን በማካተት የሚሻል ሲሆን በቀጣይም ከሰንበት ት/ቤቱ የሌሎች ክፍሎች አሠራር መመሪያዎች ጋር እየተናበበ እንደሚተገበር ታውቋል።

በመመሪያው ዝግጅት የተሳተፉትን ሁሉ ከአጥቢያ ዶት ኮም እንኳን ደስ አላችሁ የሚል መልእክታችንን እናስተላልፋለን።

ውጤታማ የስራ አመራር ስልጠና በሸገር ከተማ ሃገረ ስብከት ደ/ኃ/ቅ/ሚካኤል ካቴድራል ፍሬ ስብሐት ሰ/ት ቤት ተሰጠ

ነሐሴ 5 ቀን 2016 ዓ.ም.

የማኅበረ ቅዱሳን የ2016 ዓ.ም. ግቢ ጉባኤያት ተመራቂዎች ዲጅታል መጽሔት ስራ ተጠናቀቀ

በአጥቢያ ዶት ኮም ፕሮጀክት ተቋራጭነት የተሰራው የዚህ አመት (2016) የግቢ ጉባኤያት ተመራቂዎች ዲጅታል መጽሔት ስራ ከታቀደለት የጊዜ ሰሌዳ አስቀድሞ ትናንት ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም.  የተጠናቀቀ ሲሆን የዲጅታል የምረቃ መጽሔቱ ለተመራቂዎች በስርጭት ላይ ይገኛል። የአመቱን የተመራቂዎች ዲጅታል መጽሔት በማስመልከት የግቢ ጉባኤያት ማስተባበሪያው የማስተዋወቂያ መርሐግብር እንደሚያዘጋጅ ታውቋል።

አጥቢያ ዶት ኮም ለፕሮጀክቱ መሳካት አስተዋጽዖ ያደረጉ የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት አስተባባሪዎች (በሁሉም እርከን ላይ የሚገኙ) ከፍ ያለ ምስጋናን ያቀርባል።

 

ውጤታማ የስራ አመራር ስልጠና በኦስሎ ማህደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ተሰጠ

በኦስሎ ማህደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ለአምስት ተከታታይ ሳምንታት በበይነ መረብ የተሰጠው የውጤታማ ስራ አመራር ስልጠና በትናንትናው ዕለት ሚያዝያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ተጠናቀቀ። በስልጠናው የተካተቱ የይዘት አርእስት የኢ/ኦ/ተ/ቤ፣ ባህል እና የለውጥ አመራር፣ ውጤታማ ተግባቦት፣ ውጤታማ ስብሰባ፣ በእቅድ መመራት፣ የአሰራር መመሪያ ዝግጅት እና ውጤታማ የጊዜ አጠቃቀም ሲሆኑ ስልጠናው በአጥቢያ ዶት ኮም ባለሞያዎች በሚሰጥ ገለጻ፣ ሰልጣኞችን ያሳተፈ ውይይት እና ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን ያካተተ እንደነበረ ታውቋል።

የደብሩ አስተዳዳሪ ቀሲስ ተስፋ ሚካኤል መኮንን በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ ገልጸዋል። ስልጠናው ብዙ ክህሎቶችን ያስጨበጠ ሲሆን በቀጣይም ወደ ትግበራ በመቀየር የአሰራር ማሻሻያዎችን ማስመግዘብ ይገባናል ብለዋል። በተጨማሪም በጅማሮ ላይ ያለው የደብሩ ስልታዊ እቅድ ዝግጅት ከአጥቢያ ዶት ኮም በሚደረገው ሞያዊ ድጋፍ የደብሩን ማኅበረሰብ አሳታፊ በሆነ መልኩ በልጽጎ ስራ ላይ እንዲውል እንሰራለን ብለዋል።

አጥቢያ ዶት ኮም በቀጣይ የክፍሎች አሰራር መመሪያዎች ዝግጅት እንዲሁም የቴክኖሎጂ ክፍልና የማዋቀር እና ስራ የማስጀመር ፕሮጀክቶችን ከደብሩ ሰበካ አስተዳደር ጉባኤ ጋር በመሆን የሚተገብር መሆኑም ተገልጿል።

ለሊቨርፑል መካነ ቅዱሳን አቡነ ተክለ ኃይማኖት ቤ/ክ የተሰጠው የውጤታማ ሥራ አመራር ስልጠና ተጠናቀቀ

ለሰባት ተከታታይ ሳምንታት በበይነ መረብ የተሰጠው የውጤታማ ሥራ አመራር ስልጠና በትናንትናው እለት ተጠናቅቋል። በስልጠናው የተለያዩ መሰረታዊ ጉዳዮች የተዳሰሱ ሲሆን ስልጠናው በገለጻ፣ ውይይት እና ተግባራዊ እንቅስቃሴ የተደገፈ እንደነበር ታውቋል። የተሸፈኑት ዋና ዋና አርእስት፦ የኢ/ኦ/ተ/ቤ፣ ባህል እና የለውጥ አመራር፣ ባህል እና የለውጥ አመራር፣ ውጤታማ ተግባቦት፣ ውጤታማ ስብሰባ፣ በእቅድ መመራት እና የአሰራር መመሪያ ዝግጅት እንደሆኑ ታውቋል።

በመርሐግብሩ ማጠቃለያ ላይ የደብሩ አስተዳዳሪ ሊቀትጉኃን ቀሲስ ብርሃኑ ደሳለኝ ይህ የሰበካ አስተዳደር ጉባኤ እድለኛ ነው። ውጤታማ ሥራን ለመስራት እና የበለጠ ለማገልገል የሚረዱ ክህሎቶችን ያስተዋወቀ ስልጠና አግኝቷል ብለዋል። እንዲሁም ለመርሐግብሩ ዝግጅት ቁልፍ የማስተባበር ስራን የሰሩት ቀሲስ ተመስገን ቅጣው ሰልጣኞች በስልጠናው ያገኟቸውን እውቀቶች በስራ ለመተግበር ሶስት ነገሮች ፡- ቁርጥ ውሳኔ፣ ትግበራ እና የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን መሻገር፣ ወደቀደመ አሰራሮች ላለመመለስ መታገል ያስፈልጋል ብለዋል

በመርሐግብሩ መዝጊያ ላይ አጥቢያ ዶት ኮም የስልጠናውን ቀጣይ ትግበራ የማገዝ እና የመከታተል ስራን የሚሰራ ሲሆን በቀጣይነትም ሌሎች ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ መርሐግብሮች ቀርጾ እንደሚንቀሳቀስ ተገልጿል።

የድረገጽ አስተዳደር ሥልጠና ለትሮንዳሔም ምሥራቀ ፀሐይ ቅ/ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ተሰጠ

መጋቢት 20፣ 2016 ዓ.ም.

በኖርዌይ አገር ትሮንዳሔም ከተማ የሚገኘው የምሥራቀ ፀሐይ ቅ/ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የቴክኖሎጂ ክፍልን በማቋቋም አሰራሮችን የማዘመን እና በቴክኖሎጂ የማስደገፍ እንቅስቃሴዎችን ጀምሯል። የዚህ እንቅስቃሴ አካል ከሆኑት ተፈጻሚዎች አንዱ በአጥቢያ ዶት ኮም ለብዙ አመታት በሙሉ ድጋፍ ሲተዳደር የነበረውን ድረገጽ የሚያስፈልገውን ስልጠና በመውሰድ በደብሩ ባለሞያዎች የማስተዳደር ስራ ነው። በዚሁም መሰረት በትናንትናው እለት (መጋቢት 20፣ 2016 ዓ.ም.) ለቴክኒክ ቡድኑ የመነሻ ስልጠና ተሰጥቷል።

በስልጠናው የይዘት አስተዳደር ሒደት እንዲሁም መረጃዎችን በድረገጹ የመለጠፍ፣ የማስተዋወቅ እንዲሁም የማንሳት በተግባር በመደገፍ ተካሒዷል። በቀጣይም በደብሩ የሚተገበሩ ልዩ ልዩ የቴክኖሎጂ ተፈጻሚዎች ሲኖሩ አጥቢያ ዶት ኮም በአማካሪነት እና ድጋፍ ሰጭነት የደብሩን አቅም የማጎልበት ስራን እንደሚሰራ ታውቋል።

አገልጋይ የቴክኖሎጂ ባለሞያዎችን የማፍራት ስራ /Incubation Program/ የሙከራ ትግበራ ጀመረ

አጥቢያ ዶት ኮም ተተኪ ባለሞያዎችን ለማፍራት እና የአገልግሎቶችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚያስችል የማብቂያ መርሐግብር /Incubation Program/ የሙከራ ትግበራ ጀምሯል። በዚህ የሙከራ ትግበራ ተሳታፊዎችን ከሰንበት ት/ቤቶች አንድነት እና ከማኅበረ ቅዱሳን ግቢ ጉባኤያት ማስተባበሪያ በተሰጡ የተሳታፊ ጥቆማዎች መነሻነት ምልመላ የተደረገ ሲሆን መርሐግብሩ ከ3-6 ወራትን የሚፈጅ ይሆናል።

የመርሐግብሩ ተሳታፊዎች በቴክኖሎጂ፣ ተቋማዊ አሰራር እና መፈሳዊ የሞያ አገልግሎት ዙርያ ስልጠናዎችን የሚወስዱ ሲሆን በአጥቢያ ዶት ኮም ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች በመሳተፍ ተግባራዊ ልምምድ እንደሚያደርጉ ታውቋል።

የኦስሎ ማህደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ድረገጽ በአዲስ መልክ ተሻሽሎ ተለቀቀ!

የኦስሎ ማህደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ድረገጽ በአዲስ መልክ ተሻሽሎ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት በዓል ምክንያት በማድረግ ተለቅቋል። ድረገጹን ይህንን በመጫን ይመልከቱ

ድረገጹ በአጥቢያ ዶት ኮም ከተሰሩ ሌሎች የቤተርክርስቲያናችን ድረገጾች ጋር ወጥነትን ጠብቆ የተሰራ እንደሆነ ታውቋል። በቀጣይም ከድረገጽ ባለፈ የደብሩን አሰራሮች በቴክኖሎጂ የማስደገፍ ስራዎች እንደሚሰሩ ታውቋል።